አዲስ አበባ | መስከረም 24 ቀን 2019 ዓ.ም

የዘውዲቱ መሸሻ የህጻናትና ቤተሰብ የበጎ አድራጎትና ልማት ማህበር መስራች የሆኑት እመበረከት ዘውዲቱ መሸሻ 85ኛ የልደት በዓላቸው የረጅም ዓመታት የበጎ አድራጎት አስተዋጽኦአቸውን፣ ለህጻናትና ለተቸገሩ ወገኖች ያደረጉትን የላቀ ውለታ በሚያስታውስ መልኩ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

በዓሉ በብጹዕ አቡነ ፊሊጶስ የደቡብ ኦሞ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፣ መጋቢ ሀዲስ እሸቱ፣ የክብር እንግዶች፣ የድርጅቱ ደጋፊዎች፣ ሰራተኞች እና በማዕከሉ ህጻናት ተሳትፎ በደስታና በፍቅር ተከብሯል። የተለያዩ የማህበረሰቡ አካላት በተገኙበት የተካሄደው ይህ ልዩ በዓል፣ ለመስራቿ ያለውን ክብር፣ ፍቅርና አድናቆት የገለጸ የደስታ ቀን ሆኖ አልፏል። በዚሁ እለት በተለያዩ የሙያ ዘርፍና ደረጃ የተመረቁ ተማሪዎች፣ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ልጆች የዕውቅናና የሽልማት ስነ ስርዓት በማርያም ወዳጆች ተካሂዷል፡፡

እመበረከት ዘውዲቱ መሸሻ በረጅም ዓመታት የበጎ አድራጎት ተግባራቸው ለብዙ ህጻናት የተስፋ፣ የእንክብካቤና የአዲስ ሕይወት መሠረት ለመሆን ችለዋል። የህጻናትን ደህንነት፣ እድገትና የወደፊት ሕይወት ለማሻሻል ያደረጉት ጥረት ለብዙዎች አርአያ የሚሆን የሰብዓዊነትና የርህራሄ ተግባር ነው።

በዓሉ የመስራቿን የሕይወት ጉዞና የበጎ አድራጎት አሻራ ከማስታወስ ባሻገር፣ ለህጻናት ደህንነትና ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ በጋራ መቆም ያለውን ትልቅ ፋይዳ የሚያሳይ አጋጣሚ ነበር።

ድርጅታችን በበዓሉ በመገኘት ደስታቸውን ለተጋሩ፣ ለመስራቿ ክብር ለሰጡ እንግዶች፣ ለደጋፊዎች፣ ለሰራተኞችና ለሁሉም ተሳታፊዎች ልባዊ ምስጋናውን ያቀርባል።

እመበረከት ዘውዲቱ መሸሻ እንኳን ለ85ኛ የልደት በዓልዎ አደረስዎ! ረጅም ዕድሜ ከጤና፣ ከሰላም፣ ከደስታና ከበረከት ጋር እንዲሰጥዎ እንመኝልዎታለን።

ለበለጠ መረጃና ድጋፍ ለማድረግ፦

Websit: https://zewditumeshesha.org/

Telegram: t.me/+pMFeQ3LZ-WliNmRk

YouTube: youtube.com/@ZEWDITUASSOCIATION

TikTok: tiktok.com/@zewditumesaha