አዲስ አበባ | መስከረም 5 ቀን 2019 ዓ.ም

ዘውዲቱ መሸሻ የህፃናትና ቤተሰብ የበጎ አድራጎትና ልማት ማህበር በማዕከሉ የሚገኙ ልጆች ከዕለት ተዕለት ተግባራቸው ጎን ለጎን ትምህርት ከመጀመሩ በፊት በአዲስ አዕምሮ እንዲቀበሉ ይረዳቸው ዘንድ እና ዕረፍት እንዲያገኙ፣ በደስታና በመዝናናት ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ የሚያስችል የመዝናኛና የጉብኝት ፕሮግራም አዘጋጀ።

በፕሮግራሙ ላይ የማዕከሉ ልጆች፣ የፕሮግራም አስተባባሪዎችና አስተዳደር ሰራተኞች በመሳተፍ የተለያዩ የመዝናኛ፣ የጨዋታና የጉብኝት ተግባራትን አከናውነዋል። ፕሮግራሙ ልጆቹ ከጓደኞቻቸው ጋር በመዝናናት፣ በመጫወትና አዳዲስ ልምዶችን በማግኘት ደስታቸውን እንዲጋሩ ዕድል ፈጥሯል።

የጉብኝቱ አካል የሆነው ፕሮግራም ልጆቹ ከማዕከሉ ውጭ ያለውን አካባቢ በመመልከትና በመጎብኘት አዳዲስ ነገሮችን እንዲማሩ፣ የጋራ ተሳትፎና የጓደኝነት ስሜታቸውን እንዲያጠናክሩ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ተብሎ ይታመንበታል።

የድርጅቱ አመራር እንደገለጸው፣ እንደዚህ ያሉ የመዝናኛና የጉብኝት ፕሮግራሞች ለልጆች የደስታ ጊዜን ከመፍጠር ባሻገር በስነ-ልቦና፣ በማህበራዊ ተሳትፎና በግል እድገታቸው ላይ ጠቃሚ ሚና ይኖረዋል።

የድርጅቱ ልጆች በደህንነት፣ በፍቅርና በደስታ እንዲያድጉ ከመደበኛ የእንክብካቤ፣ የትምህርትና የጥበቃ አገልግሎቶች ጎን ለጎን የመዝናኛና የልማት ፕሮግራሞችንም ማጠናከር እንደሚቀጥል ተገልጿል።